የትምህርት ዓላማዎች
በዚህ ትምህርት መጨረሻ ተማሪው የሚከተሉትን ማድረግ ይኖርበታል፦
(1) የእግዚአብሔርን የትዳር ንድፍ እና አላማ መቀበል።
(2) የሴቶችን ዋጋ በእግዚአብሔር እይታ መረዳት።
(3) ለክርስቲያናዊ ጋብቻ የእግዚአብሔርን መመሪያዎች በግል ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ።
Lesson
Playlist
Search through all lessons and sections in this course
Searching...
No results found
No matches for ""
Try different keywords or check your spelling
1 min read
by Stephen Gibson
በዚህ ትምህርት መጨረሻ ተማሪው የሚከተሉትን ማድረግ ይኖርበታል፦
(1) የእግዚአብሔርን የትዳር ንድፍ እና አላማ መቀበል።
(2) የሴቶችን ዋጋ በእግዚአብሔር እይታ መረዳት።
(3) ለክርስቲያናዊ ጋብቻ የእግዚአብሔርን መመሪያዎች በግል ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ።
Hernando Cortes በባህሪው እና በፍላጎቱ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ አይደለም። ሆኖም ከድርጊቶቹ አንዱ ለግቦቹ ሙሉ ቁርጠኛ እንደሆነ አሳይቷል። በ1519 የጸደይ ወራት Hernando Cortes በአሁኑ ጊዜ ሜክሲኮ እየተባለ የሚጠራውን ግዛት ለመቆጣጠር አንድን ጉዞ መርቷል። የስፔን ገዥ በ11 መርከቦች እና በ700 ሰዎች ለተልእኮው ድጋፍ አድርጓል። Cortes እና ሰዎቹ ለወራት በባህር ላይ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ሜክሲኮ ዳርቻ ደረሱ። ቀጣዩ ፈተና በየብስ ወደ ዋና ከተማው መጓዝ ነበር። Cortes በምድር ላይ የሚደረገው ጉዞ አስቸጋሪ እና አደገኛ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። ሰዎቹ ወደ ኋላ መመለሳቸው አማራጭ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡት ስለፈለገ መርከቦቹን በሙሉ አቃጠለ። ወደ ስፔን መመለስ የማይቻል ሲሆን ይህ ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ ስኬታማ ለመሆን ኃይለኛ ተነሳሽነትን ፈጠረ። እንደዚሁም ሁሉ ወደ ትዳር የሚገቡት ሰዎች በትዳር ውስጥ ሲገቡ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በመገንዘብ ፍፁም ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጋብቻ ውብ ነገር ነው።[1] ነገር ግን ውበቱን ለመቅመስ እና መልካሙን ለማየት የሚፈልጉ ጥንዶች መፅሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን በመመርመር ከዚያም ለተማሩት መታዘዝን መከተል አለባቸው። የሚያረካ ትዳር ጥረትና መሥዋዕትነትን ይጠይቃል።
► ስለሚያስፈልገው ቁርጠኝነት ሳያውቅ አንድ ሰው እርሱ/ሷ ጥቅማ ጥቅሞችን ብቻ እየጠበቀ/ች ወደ ትዳር እንዴት እንደገብ ማካፈል የሚችል አለን?
ጋብቻን ለመረዳት ወደ መጀመሪያው ወደ ዘፍጥረት መመለስ አለብን። የፍጥረት ታሪክ ስለ ጋብቻ ያስተምረናል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጋብቻ ለኅብረት ነው።
“ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ፣ ‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ’ አለ” (ዘፍጥረት 2፥18)።
እግዚአብሔር አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በኅብረት እንደሆነ ሁሉ እግዚአብሔርም ማኅበራዊ እንድንሆን አድርጎ ፈጠረን። ለውይይት ነው የተፈጠርነው። የተፈጠርነው ለመቀራረብ እና ለኅብረት ነው። እግዚአብሔር ለብቻ መሆን ጥሩ እንዳልሆነ ተናግሯል።
የዘፍጥረት እያንዳንዱ የክስተቶች ዘገባ ለትዳር ክብርን ይሰጣል። እግዚአብሔርም ከወንዱ የጎድን አጥንት ወስዶ ቆንጆ ሴት አድርጎ ሰራት፣ በእግዚአብሔር መልክ በእኩል የተሠራ ሌላ ሰው፣ በዋጋው እኩል የሆነ፣ በንድፍ ግን የተለየ፣ ሰውንም ፍፁም ሙሉ አደረገው። እርሷ በተለየ ክብር “የፈጣሪ የመጨረሻ እና ፍፁም ስራ ሆና ለሰው ተሰጥታለች።”[1]
ትዳር አስደሳች ኅብረት መሆን ነው።
አዳም “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ” (ዘፍጥረት 2፥23) ሲል አክብሮትንና ደስታን ይገልጽ ነበር። አዳም “በመጨረሻም ባሪያ አገኘው። አሁን ልብሶቼን የሚያጥብ፣ ምግቤን የሚያበስልልኝ፣ ጀርባዬን የሚያሽ እና የቤት ውስጥ ስራዬን የሚሰራ ሰው አለኝ” አላለም። አዳም “በመጨረሻም ሙሉ የሚያደርገኝ ረዳት” አለ።
ጋብቻ የእኩልነት ህብረት መሆን ነው።
“...የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” (ዘፍጥረት 2፥18)። እግዚአብሔር ሴትን ፍጹም እንድትመሳሰል እና ሰውን እንድትሞላ አድርጎ ፈጠረ።
Matthew Henry እንዲህ በማለት ያሳስበናል “ሴቲቱ ከአዳም ጎን የጎድን አጥንት ተሠራች፣ በእርሱ ላይ ለመግዛት ከጭንቅላቱ አልተፈጠረችም፣ በእርሱ ላይ ለመራመድ ከእግሮቹ አልተፈጠረችም፣ ነገር ግን ከእርሱ ጋር እኩል ትሆን ዘንድ ከጎኑ ተፈጠረች፣ በክንዱ ስር እንድትጠበቅ እና እንድትወደድም ከልቡ አጠገብ”። ሴት ከወንድ ያላነሰችም ሆነ የበላይ ሆና አልነበረም ነገር ግን ከእሱ ጋር የምትወዳደር ነበረች።[2]
ትዳር የቃል ኪዳን ኅብረት መሆን ነው።
“ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋራ ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ዘፍጥረት 2፥24)። ጠንካራ ትዳር በፍቅር ስሜቶች ላይ የተመካ አይደለም (የፍቅር ስሜት ይመጣል እና ይሄዳል) ወይም እርካታ (ጤናማ ትዳር ግን ደስታን ያመጣል) ወይም ግላዊ መሟላትን (ጠንካራ ትዳር በእርግጥም መሉነትን አለው)። ትዳር የሚያስገኛቸው አስደናቂ ጥቅሞች ጠንካራ ትዳርን አይፈጥሩም እነርሱ የጠንካራ ትዳር ውጤቶች ናቸው። ጋብቻ በማይናወጥ የቃል ኪዳን መሠረት ላይ ይመሰረታል። አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት አንዳቸው ለሌላው ለሕይወት ዘመን የተሰጡ ናቸው።
ጋብቻ ግልጽ፣ እምነት የሚጣልበት፣ የሚቀበል ግንኙነት መሆን አለበት “አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር” (ዘፍጥረት 2፥25)። ምክንያቱም ኃጢአት የመጀመሪያዎቹን ጥንዶች ንፁህነት ገና ስላላበላሸው ትዳራቸው ያለፍርድ፣ ያለ ኀፍረት እና ያለ ፍርሃት ነበር። አዲስ ኪዳን እንዲህ ይለናል “ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን” (ዕብራውያን 13፥4)።
ጠንካራ ጋብቻ ባለትዳሮች አንዱ ለአንዱ ለትዳር ቁርጠኝነት እርግጠኛ ባልሆኑበት አለመረጋጋት፣ አለመተማመን፣ ጥርጣሬ ወይም ፍርሃት ባለበት ሊኖር አይችልም። ጠንካራ ጋብቻዎች አንዱ የትዳር ጓደኛ ሲሞት ብቻ የሚያበቃ የጸና ቃል ኪዳን ያስፈልጋቸዋል (ሮሜ 7፥1-2)።
የእግዚአብሔር ሐሳብ ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የዕድሜ ልክ ቃል ኪዳን እንዲሆን ነው (ማቴዎስ 19፥3-6)። ጳውሎስ አማኞች ያላመኑት የትዳር ጓደኞቻቸው ከእነርሱ ሲለዩ በእስር ውስጥ እንደማይገኙ ተናግሯል (1ኛ ቆሮንቶስ 7፥15) ነገር ግን አማኝ ከማያምን የትዳር ጓደኛ መለየት የለበትም (1ኛ ቆሮንቶስ 7፥12-14፣ 16)። ጳውሎስ ቀደም ሲል ጌታ በተመሳሳይ እንደተናገረ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ አማኞች ከትዳር ጓደኞቻቸው ለመውጣት/ለመለያየት አይምረጡ፤ ይህን ካደረጉ ግን ሌላ ማግባት የለባቸውም (1ኛ ቆሮንቶስ 7፥10-11፣ ማቴዎስ 5፥31-32፣ ማቴዎስ 19፥9)።
የቃል ኪዳን ፍቅር ራስን መስጠት፣ መከባበር እና ግንኙነቱ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም የሚያስጌጥ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 13)። ደካማ ቁርጠኝነት ጊዜያዊ ጥረትን፣ የስሜት መለያየትን፣ መራቅን እና ፈተናን ይፈጥራል።
ባል ለሙሽሪት ምላሽ በማትሰጥ ወይም በአክብሮት በማትሆን ወይም በታመመች ጊዜ እንኳ ተስፋ ሳይቆርጥ በኪዳናዊ ፍቅር እየኖረ ነው። ሚስት ለክርስቶስ ስትል ባሏን ለማክበር እና ለመታዘዝ ስትመርጥ፣ ባሏ ባልወደዳትም ጊዜ በኪዳናዊ ፍቅር እየኖረች ነው።
ፍቅሩ ክብሯን ያነሳሳል እና ክብሯም ፍቅሩን ያነሳሳል። እና እድገታቸውን ይቀጥላሉ።
► ሰዎች በትዳራቸው ደስተኛ ካልሆኑ በኋላ ላይ ውሳኔያቸውን መቀየር እንደሚችሉ በማሰብ ቢያገቡ ምን ችግሮች ይከሰታሉ? አንድ ሰው ጋብቻው ዘላቂ ነው ብሎ ሲያምን ሙሉ በሙሉ ቃል መግባቱ ምን ለውጥ ያመጣል?
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጋብቻ የፍጥረት ቦታ ነው፡ የመራቢያ ቦታ ነው።
“እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው” (መዝሙረ ዳዊት 127:3)።
ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው ነገር ግን በተመሳሳይ መልኩ ከወላጆች ለእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎችም ናቸው። “እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? በሥጋም በመንፈስም የርሱ ናቸው። ለምን አንድ አደረጋቸው? ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ዘር ይፈልግ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋራ ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ” (ሚልክያስ 2፥15)። እግዚአብሔር አምላክን የሚፈሩ ልጆችን የሚፈልገው ከአማኝ ባልና ሚስት አንድነት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ልጆችን የማያካትተውን የአኗኗር ዘይቤ መከተል ይመርጣሉ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች አምላካዊ ልጆች ሲወልዱ እግዚአብሔር እንደሚደሰት ያስተምራል።
እግዚአብሔር የሚፈልገው መራባት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚፈሩ ልጆች መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ወላጆች ልጆቻቸው ክርስቶስን እንዲከተሉ እንዲያስተምሩ በእግዚአብሔር ተጠርተዋል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጋብቻ ለክርስቶስ ነው
በኤፌሶን 5፥30-32 መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ የተደበቀውን ጥልቅ የትዳር ትርጉም ገልጧል። ጋብቻ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቤተክርስቲያኑ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ ምድራዊ ምስል ነጸብራቅ ነው።
ጳውሎስ ይህንን ክፍል የጀመረው አማኞች በመንፈስ እንዲሞሉ በማሳሰብ ነው (ኤፌሶን 5፥18)። ስለ ጋብቻ የሚከተለውን መመሪያ የሰጠው በዚህ አውድ ነው።
በመንፈስ የተመላችው ሙሽራ ለባልዋ (“የእርሷ ራስ ለሆነው”) በጌታ ትገዛለች፣ ልክ አማኞች ለኢየሱስ እንደሚገዙ (ኤፌሶን 5፥24፣ 32፤ በተጨማሪም 1ኛ ጴጥሮስ 3፥1 ተመልከቱ)። ለኢየሱስና ለባሏ አክብሮት የምታሳይበት መንገድ ይህ ነው።
ለእያንዳንዱ ሚስት በመገዛቷ ላይ ጌታን በልቦናዋ ማኖሯ አስፈላጊ ነው። እርሷ የምትገዛለት ባል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለርሱ እና ለእርሱ ነው። ዓይኗ በኢየሱስ ላይ ነው እርሱ ብቻውን ነውር የሌለበት ነው። ሚስት ለባልዋ በፈቃደኝነት መገዛቷ ለኢየሱስ አምልኮ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገዛት፣ ልክ እንደ ፍቅር፣ በግድ አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገዛት ሚስቶች ክርስቶስን ለማክበር ለባሎቻቸው የሚያቀርቡት ስጦታ ነው (ኤፌሶን 5፥33)። በሁሉም ነገር መገዛት ለኢየሱስ አምልኮ ነው።[3]
ሚስት ለባልዋ መገዛቷ ለእርሱ አክብሮት ነው (ቁጥር 33) በመንፈስ የተሞላ ሕይወት አካል ነው (ኤፌሶን 5፥18-21)። ከገርና ከዝግተኛ መንፈስ የሚገኘው ይህ ክብር በእግዚአብሔር ፊት እጅግ የከበረ ነው (1ኛ ጴጥሮስ 3፥4-5)።
በመንፈስ የተሞላው ሙሽራ ኢየሱስ ቤተክርስቲያኑን እንደሚወድ ሙሽራውን ይወዳታል (ኤፌሶን 5፥25)። ሙሽራው የራሱን አካል እንደሚወድ ሊውዳት ይገባል (ኤፌሶን 5፥28-29)። ለእርሷ ሲል ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ኢየሱስ ለቤተክርስቲያኑ እንደገለጠው በመንፈስ የተሞላ የራስን ጥቅምን መስዋዕት ማድረግን ማሳየት አለበት። ይህ የእርሱ የመገዛት ተግባር ነው (ኤፌሶን 5፥21)። አንድ አስተያየት ሰጪ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፦
እርሱ (ኢየሱስ) ቤተክርስቲያንን ለማዳን በመስቀል ላይ መከራን ለመቀበል ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ፣ እኛም ራሳችንን ለመካድ ድካማችንን እና ፈተናን ለመሸከም ፈቃደኞች መሆን አለብን፣ በዚህም የሚስትን ደስታ እናበረታታለን። ለእሷ ድጋፍ መትጋት የባል ግዴታ ነው፣ ፍላጎቱዋን ማሟላት፣ አስፈላጊ ከሆነ እረፍት እና ምቾቱን በመተው በህመሟ ጊዜ መርዳት፣ በአደጋ ጊዜ ከእርሷ ፊት መሆን እና መከላከል፣ እርሷ ስትቆጣ በመታገስ፣ በገፋችውም ጊዜ ከእርሷ ጋር በመጣበቅ መቆም፣ በመንፈሳዊ ችግር ውስጥ እያለች ከእሷ ጋር መጸለይ፣ እና እርሷን ለማዳን ለመሞት ዝግጁ መሆን አለበት። ይህ ለምን መሆን የለበትም? መርከባቸው ቢሰበር እናም ለድህነት የሚሆን አንድ ሳንቃ ቢኖር እርሷን በዚያ ላይ ሊያስቀምጣት እና ለራሱ ከአደጋ ሊጠብቃት አይሻምን? ነገር ግን ሌላም ነገር አለ፤ ባል የሚስቱን መዳን መፈለግ በህይወቱ ውስጥ ዋነኛው ነገር እንደሆነ ሊሰማው ይገባል። ለነፍሷ የምትፈልገውን ሁሉ ያዘጋጅላታል። በዚህም ምሳሌ መሆን፤ ምክር ቢያስፈልጋት ለመምከር እና የመዳንን መንገድ በተቻለ መጠን ለእርሷ ቀላል ማድረግ አለበት። አንድ ባል የአዳኙ መንፈስ እና ራስን የመካድ መንፈስ ካለው የቤተሰቡን መዳን ለማስፋት ቢችል ምንም ዓይነት መሥዋዕትነትን እንደ ትልቅ ነገር አይቆጥርም።[4]
ክርስቶስ ሙሽራውን ቤተክርስቲያንን እንዳነጻ ሙሽራው የሙሽራይቱን ንፅህና መፈለግ አለበት “በቃሉ አማካይነት በውሃ ዐጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ እንዲሁም ጕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና እንከን አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው” (ኤፌሶን 5፥26-27)።
በጥንት ጊዜ የንጉሣውያን ሙሽሮች በአካል ውድ በሆኑ የውበት መጠበቂያዎች ይነጻሉ “ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ ልዩ ልዩ ሽቱ በመቀባትና…” (አስቴር 2፥12ን ተመልከቱ)። በዚህ መንገድ ድንግል ለባልዋ ተዘጋጅታለች።
በመንፈሳዊ ሁኔታ፣ ባል ለሚስቱ እድገት አስፈላጊ የሆኑትን መንገዶች ሁሉ ማለትም ታማኝነት፣ ገደብ የለሽ ፍቅር፣ መረዳት፣ ጸሎት፣ ምክር፣ ትምህርት እና ደግነትን ማቅረብ አለበት።
ባል ሚስቱን እንዲህ ባለው ፍቅር ሲይዝ በደስታ ይከፈለዋል። ጳውሎስ “ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወድዳል” (ኤፌሶን 5፥28) ብሏል። በዚህ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንገድ ሚስቶቻቸውን የሚወዱ ባሎች በጌታ ከሚከፈላቸው በላይ ከሚስታቸው አክብሮት፣ ፍቅር እና ታማኝነትን ሊያገኙ ይችላሉ።
► አንድ ባል ለሚስቱ መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ምን ማድረግ ይኖርበታል?
(1) የእግዚአብሔርን የመጀመሪያ ንድፍ ማክበር እና በትዳር ውስጥ ያላቸውን ልዩ ሚና ማድነቅ አለባቸው።
ባል ሚስቱ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኗን፣ እርሱን መሉ የምታደርግ ረዳት መሆኗን ማስታወስ አለበት። ለደህንነቷ እና ለእርሷ መንፈሳዊ፣ ስሜታዊ እና አካላዊ ደህንነት ሲል ህይወቱን አሳልፎ መስጠት አለበት። በእርሷ ውስጥ መለወጥ የሚገባውን መለወጥ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለእርሷ ምስጋናን መምረጥ እና እርሷ የማይገባት በሚመስል ጊዜም ቢሆን መውደድ አለበት። እግዚአብሔርም ታዛዥነቱን እና እምነቱን ያከብራል።
ሚስት እግዚአብሔር ባሏን እንደ ራስ አድርጎ ስለመረጠው ማክበር፣ በምትችለው መንገድ ሁሉ ለእርሱ አክብሮት ማሳየት እና አመራሩን ማክበር አለባት። እርሱ ስህተት በሚሠራበት ጊዜ እና ምንም የማይገባው ሲመስልም እግዚአብሔር በእርሱ መለወጥ ያለበትን እንዲለውጥ በመጸለይ መገዛትን እና አክብሮትን መምረጥ አለባት። እግዚአብሔርም ታዛዥነቷን እና እምነትዋን ያከብራል።
(2) ባለትዳሮች እውነተኛ መንፈሳዊ እና አካላዊ ቅርርብን ማዳበር አለባቸው።
ያለ ፍርሃት፣ ነቀፌታ፣ ከሌሎች ጋር ንጽጽር፣ ስድብ፣ ፍትወት፣ ራስን ከማድነቅ፣ ወይም ማዋረድ ሳይኖር እርስ በርስ ለመተዋወቅ መፈለግ አለባቸው። በእግዚአብሔር ፊት እና እርስ በርስ በግልፅነት እና በቅንነት መኖር አለባቸው።
(3) ባለትዳሮች ማድረግ የሚገባቸውን ማድረግ ሲያቅታቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ ምሳሌ መከተል አለባቸው።
አዳምና ሔዋን በኃጢአት ሲወድቁ ባፈሩ እና በተጸጸቱ ጊዜ እግዚአብሔር ውድቀታቸውን ለመቤዠት ኃይሉን ገለጠ። እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ኀፍረተ ሥጋን መሸፈኛ ልብስ ይሠራላቸው ዘንድ እንስሳን ሠዋ (ዘፍጥረት 3፥21)። ይህ የእግዚአብሔር የፍቅር ተግባር የጸጋ ምስል እና እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የመቤዠት ተስፋ ነው። ክርስቶስ ይቅር እንድንባል እና እንድንታደስ ያደርገናል። በክርስቶስ በኩል፣ ባለትዳሮች ከወደቁ በኋላም ያለምንም እፍረት ወደ ወዳጅነት መመለስ ይችላሉ።
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በሮማውያን ዓለም እና በአይሁድ እምነት ሴቶች ከወንዶች ያነሱ ተደርገው ይታዩ ነበር። በሴቶች ላይ ያለው ዝቅተኛ አመለካከት አሁንም በአለም ዙሪያ ባሉ በብዙ ባህሎች እና በብዙ ቤቶች ውስጥ ተስፋፍቶ ይገኛል። ሴቶች አይከበሩም፣ እንደ ወሲባዊ ዕቃ ይጠቀሙባቸዋል እና ጥቃት ይደርስባቸዋል። ነገር ግን ኢየሱስ ለሴቶች ያለው ከፍ ያለ ግምት ምሳሌያችን ሊሆን ይገባል።
ለክርስቶስ ሴቶች ከወንዶች እኩል ክብር እና ዋጋ አላቸው። ኢየሱስም “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን?” ሲል ጠየቀ። (ማቴዎስ 19፥4፣ ዘፍጥረት 1፥27)። ሴቶች እንደ ወንዶች በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል። እንደ ወንዶች እራስን ማወቅ፣ የግል ነፃነት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መለኪያ እና ለድርጊታቸው ግላዊ ሃላፊነት አላቸው። ሴቶች በኢየሱስ ዘንድ እንደ እውነተኛ ሰዎች ይመለከታቸዋል እንጂ እንደ ወንድ የምኞት ዕቃ ብቻ አይደለም። ወደ ዓለም እንደ መጣላቸው ሰዎች ይመለከታቸው ነበር (ሉቃስ 8፥1-3)።
James Borland ከJohn piper እና Wayne Grudem ጋር በአራቱ ወንጌላት ውስጥ የሚገኙትን ኢየሱስ ለሴቶች ያለውን ከፍ ያለ አመለካከት እና ለሴቶች ያለውን ክብር የሚያሳዩ ግልጽ ምሳሌዎችን አቅርበዋል፦
(1) ኢየሱስ በአደባባይ እያለ ሴቶችን አዘውትሮ ይናገር ነበር።
በኢየሱስ ዘመን ይህን ማድረግ ያልተለመደ ነበር (ዮሐንስ 4፥27)። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ሲነጋገር ሲያዩ ተገረሙ (ዮሐንስ 4፡7-26)። በዝሙት ከተያዘችው ሴትም ጋር በነፃነት ተነጋገረ (ዮሐንስ 8፥10-11)። ሉቃስ ኢየሱስ የናይንን መበለት በይፋ እንዳነጋገረ ተናግሯል (ሉቃስ 7፥12-13)፣ የደም መፍሰስ ችግር ያለባት ሴት (ሉቃስ 8፥48፣ ማቴዎስ 9፥22፣ ማርቆስ 5፥34) እንዲሁም ከሕዝቡ መካከል የጠራችውን ሴት (ሉቃስ 11፥27-28) እንደተናገረ ሉቃስ ገልጿል። ኢየሱስ ለ18 ዓመታት ለጎበጠችዋ ሴት (ሉቃስ 13፥12) እና በመስቀል መንገድ ላይ ለተሰበሰቡ ሴቶች ተናግሯል (ሉቃስ 23፥27-31)።
(2) ኢየሱስ ለሴቶች ያለውን አክብሮትና ከፍ ያለ ግምት ያሳየው ከእነርሱ ጋር በተነጋገረ ጊዜ ነው።
በአሳቢነት፣ በተቆርቋሪነት ስሜት ይናገር ነበር። ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ ኢየሱስ የደም መፍሰስ ችግር ያጋጠማትን ሴት እንደ “ልጅ” እንደተናገረ እና የአካል ጉዳተኛዋን ሴት “የአብርሃም ልጅ” ሲል እንደጠራት ተናግረዋል (ሉቃስ 13፥16)። ኢየሱስ እነርሱን “የአብርሃም ሴት ልጆች” ብሎ በመጥራት “ከአብርሃም ወንዶች” ጋር በእኩል መንፈሳዊ ደረጃ ላይ አስቀመጣቸው።
(3) ኢየሱስ ለኃጢአታቸው በግል ተጠያቂ በማድረግ የሴቶችን የተፈጥሮ ዋጋ ያሳያል።
ይህንንም በውኃ ጉድጓድ ከሴቲቱ ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ ይታያል (ዮሐንስ 4፥16-18)፣ አመንዝራዋ ሴት (ዮሐንስ 8፥10-11) እና እግሩን ከቀባችው ኃጢአተኛ ሴት ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ ይታያል (ሉቃስ 7፥44-50)። ኃጢአታቸው ችላ ተብሎ ሳይሆን ተጋልጦ ነበር። የእርሱ ድርጊት እያንዳንዷ ሴት የግል ነፃነት እንዳላት፣ ለምርጫዋ ተጠያቂ እንደሆነች እና በግል የኃጢአትን፣ የንስሐ እና የይቅርታ ጉዳዮችን ማስተናገድ እንዳለባት ያሳያል።
ኢየሱስ ለሴቶች ያለው ዋጋ የዛሬይቱን ቤተክርስቲያን እንዴት መምራት ይኖርበታል
ሴቶች በአገልግሎት እና በቤት ውስጥ የሚኖራቸው የተለየ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሚና ዛሬ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት እና ቤተ እምነቶች ውስጥ እየተብራራ ነው ግን መሆን ያለበትም ይህ ነው፣ የሴቶች ዋጋ እና እኩልነት በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተፈጠሩ ሰዎች በፍፁም ሊጠየቅ አይገባም። ኢየሱስ የሴቶችን ዋጋ እና ክብር እንደ ሰው አድርጎ አሳይቷል። ኢየሱስ ሴቶችን የትንሣኤው የመጀመሪያ አብሳሪዎች እንዲሆኑ አዟል (ዮሐንስ 20፥17)። ኅብረታቸውን፣ ጸሎታቸውን፣ ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን፣ የገንዘብ ድጋፍን፣ ምስክርነታቸውን ከፍ አድርጎ ተመለከተ። ኢየሱስ ሴቶችን አክብሯል፣ ሴቶችን አስተምሯል እና ሴቶችን በአሳቢነት አገልግሏል።
ለሴቶች ያለው ክብር በአዲስ ኪዳን ታይቷል
ኢየሱስ ለሴቶች ያለው አክብሮት ምሳሌ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ውስጥ ይታያል። በጼንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በወንዶችና በሴቶች ልጆች ላይ እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ ፈሰሰ (ሐዋርያት ሥራ 2፥17-18)። መንፈስ ቅዱስ አድልዎ አላሳየም።
በሮሜ 16 ጳውሎስ ፊቢን የተባለች ሴት የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንደሆነች (ቁጥር 1)፣ ጵርስቅላ እና አቂላ አብረውት በክርስቶስ ኢየሱስ ሲሠሩ አንገታቸውን ለነፍሱ አሳልፈው የሰጡ ናቸው (ቁጥር 3-4)፣ ማርያም በትጋት እንደሠራች (ቁጥር 6)፣ ጁንያ በሐዋርያት ዘንድ የታወቀች ናት (ቁጥር 7) እና ሌሎች ሴቶችንም አመስግኗቸዋል።
በ1ኛ ተሰሎንቄ ጳውሎስ እግዚአብሔር የነደፈውን የሴቶችን ርኅራኄ እና የእናቶች ፍቅር አመስግኖታል፣ “ነገር ግን እናት ልጇን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን” (1ኛ ተሰሎንቄ 2፥7)። በኤፌሶን ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አካል እንዲወዱ አዝዟል “ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ” (ኤፌሶን 5፥25፥28)። ጴጥሮስ ለባሎች እንዲህ ብሏል “በኑሯችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ ዐስቡላቸው…የሕይወትንም በረከት ዐብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥7)።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሴቶች ውድ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር እናም ወንዶች ሴቶችን እንዲያከብሩ ተምረዋል። በየቦታው ያሉ መንፈሳዊ መሪዎች ለሴቶች የሚቆሙበት እና በየባህሉ የሚደርስባቸውን በደል ለመቃወም ጊዜው አሁን ነው። ሴቶችን ፈጣሪያቸው በአምሳሉ የነደፋቸው ሰዎች አድርገን የምንመለከትበት ጊዜ አሁን ነው። በቤተክርስቲያን ወይም በቤት ውስጥ የወንድ እና የሴት ሚና ልዩነት ትምህርት ከዚህ መሰረት መጀመር አለበት አለበለዚያ ትምህርታችን ለጥቃት መንገድ ይሆናል።
ጋብቻ የእግዚአብሔር ፍጥረት እንጂ የሰው አይደለም። ስለዚህ ለትዕዛዝ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለብን እንጂ ወደ ዓለም ወይም ባህል አይደለም። ትዳራችንን እንዴት ጠንካራ፣ ዘላቂ እና የሚክስ እንደሚያደርግ እርሱ ብቻ ያውቃል። ነገር ግን ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ልንሆን የሚገባን የትዳር አጋር አንሆንም።
► ጋብቻን ለማጠናከር ቤተክርስቲያን ልታስተምረው የሚገባቸውን መርሆች አስረዳ። በአካባቢያችሁ ውስጥ በተለየ የጎደለው ግንዛቤ ምንድን ነው?
► ባሕላችሁ ሴቶችን ከወንዶች በተለየ የሚይዝበት መንገድ እንዴት ነው?
► በአገርዎ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሴቶችን ከወንዶች የሚለዩት አያያዝ እንዴት ነው? በአብያተ ክርስቲያናት እና በባህል መካከል ልዩነት አለን?
► ከኢየሱስ ምሳሌ በመነሳት ምን ዓይነት ልማዶች መለወጥ አለባቸው?
የሰማይ አባት
አስደናቂውን የትዳር ስጦታ ስለሰጠኸን እናመሰግናለን። ትዳርን ባቀድከው መንገድ እንድንለማመድ አስፈላጊውን ቃል እንድንገባ እርዳን።
በክርስቶስ እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ፍቅር የሚመስል ፍቅርን እንድናሳይ እርዳን።
እርስ በርሳችን በመከባበር ከባህላችን ግምት በላይ እንድንሄድ እርዳን።
አስደሳች፣ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር ስለሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እናመሰግናለን።
አሜን
(1) በባህልዎ ውስጥ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት በጽሑፍ ይግለጹ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በጥንቃቄ በመተግበር እነዚያ ልዩነቶች እንዴት ይሻሻላሉ?
(2) ከዚህ ትምህርት ለአንተ አዲስ የሆኑትን ሁለት መርሆች ምረጥ። እያንዳንዳቸውን በራስዎ ቃላት የሚያብራራ አንቀጽ ይጻፉ።
(3) ከታች ከተዘረዘሩት ርዕሶች በአንዱ ላይ ግልፅ ፕረዘንቴሽን አዘጋጅ። (የክፍል መሪው ርዕስ ለእያንዳንዱ ተማሪ ይመድባል።) በሚቀጥለው የክፍል ጊዜ መጀመሪያ ላይ ፕረዘንቴሽኑን ያካፍሉ።
በትዳር ውስጥ የእግዚአብሔር አንድነት ንድፍ
መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትዳር ዓላማዎች
የአንድን ሰው ትዳር ለማጠናከር የሚረዱ መንገዶች
ስለ ሴቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታ
በእግዚአብሔር በትዳር ውስጥ የተሰጡ ሚናዎች እና እነዚያን ሚናዎች ለመወጣት በመንፈስ የመሞላት አስፈላጊነት
13 lessons · አማርኛ
Your print request has been recorded. Your download should begin shortly.
Download Print-Ready FileFree to print for ministry use. No changes to content, no profit sales.
SGC exists to equip rising Christian leaders around the world by providing free, high-quality theological resources. We gladly grant permission for you to print and distribute our courses under these simple guidelines:
All materials remain the copyrighted property of Shepherds Global Classroom.
Questions? info@shepherdsglobal.org
Total
$21.99Added to Cart!
By submitting your contact info, you agree to receive occasional email updates about this ministry.
Download audio files for offline listening
No audio files are available for this course yet.
Check back soon or visit our audio courses page.
Share this free course with others