የትምህርት ዓላማዎች
በዚህ ትምህርት መጨረሻ ተማሪው የሚከተሉትን ማድረግ ይኖርበታል፦
(1) እግዚአብሔር እንዴት ውሳኔ ለማድረግ እንደሚረዳን መረዳት።
(2) የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ እና ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንዴት ዝግጁ መሆን እንደሚችሉ ማወቅ።
(3) አቅጣጫን በሚፈልጉበት ጊዜ ስህተቶችን ማስወገድ።
Lesson
Playlist
Search through all lessons and sections in this course
Searching...
No results found
No matches for ""
Try different keywords or check your spelling
1 min read
by Stephen Gibson
በዚህ ትምህርት መጨረሻ ተማሪው የሚከተሉትን ማድረግ ይኖርበታል፦
(1) እግዚአብሔር እንዴት ውሳኔ ለማድረግ እንደሚረዳን መረዳት።
(2) የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ እና ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንዴት ዝግጁ መሆን እንደሚችሉ ማወቅ።
(3) አቅጣጫን በሚፈልጉበት ጊዜ ስህተቶችን ማስወገድ።
በሴፕቴምበር 2018 ከአንድ ደሴት በታች የመሬት መንቀጥቀጥ ሱናሚ (ግዙፍ ማዕበል) አስከተለ በዚህም ወደ ፓሉ ኢንዶኔዥያ ከተማ እንዲሄድ ሆነ። ከፍ ባለ ሕንፃ ላይ ያለ አንድ ሰው ማዕበሉን ተመለከተ። ከታች በጎዳናዎች ላይ ለነበሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያን በመጮህ ተናገረ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የእርሱን ጩኸት ችላ አሉ። ከ 4,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ 10,000 ቆስለዋል።
ከአስር አመታት በፊት (2008) መንግስት ሱናሚ ከመጣ ማስጠንቀቂያ ለመላክ የተነደፉ ኤሌክትሮኒክስ ሴንሰሮች ያሉት 22 ተንሳፋፊ ነፍስ አድን በውቅያኖስ ላይ አስቀምጦ ነበር። ይሁን እንጂ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነፍስ አድን መሳሪያዎቹ አልተጠገኑምና እና ሁሉም ሥራቸውን አቁመዋል። ከመሳሪያዎቹ አንዳቸውም በ2018 ስለ ሱናሚ ማስጠንቀቂያ አልላኩም።
► በእያንዳንዱ ወታደራዊ መኪና ውስጥ የተገጠመ ነገር ምንድን ነው?
እያንዳንዱ ታንክ፣ ጂፕ እና አይሮፕላን ሬዲዮ አላቸው። ወታደሮች የሚወዱትን የሙዚቃ ጣቢያ የሚያዳምጡበት ሬዲዮ ሳይሆን የመገናኛ ሬዲዮ ነው።
ጦርነትን ለማሸነፍ መግባባት አስፈላጊ ነው። በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ወታደሮች ሙሉውን የመስክ ተግባር ማየት አይችሉም። ጓደኞቻቸው የት እንዳሉ እና ጠላቶቻቸው ደግሞ የት እንዳሉ ላያውቁ ይችላሉ። ከጦር አዛዡ ጋር በመገናኘት ካልሆነ በስተቀር ወደየትኛው አቅጣጫ መተኮስ እንዳለባቸው እና ወደየትኛው አቅጣጫ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አያውቁም።
ወታደሮች “በወዳጅ ተኩስ” የሚገደሉባቸው አጋጣሚዎችና ከወገኖቻቸው በተተኮሱ የተሳሳቱ ጥይቶች የተገደሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። በመጥፎ ግንኙነት ምክንያት ሚሳኤሎች እና ቦምቦች ከጠላት ይልቅ የገዛ ጓደኞቻቸውን የሚመቱባቸው ጊዜያት ነበሩ።
በዘመናዊ ጦርነት ውስጥ የጠላት የመገናኛ ማእከልን ለመምታት መሞከር የተለመደ ስልት ነው። ይህ የተሳካለት ወገን ጦርነቱን ያሸንፋል።
እኛ በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ ነን። ዲያብሎስ ሊፈትነን እና ሊያታልለን ይሞክራል። አለም ወደ አኗኗሩ እና እሴቶቹ ሊጎትተን ይሞክራል። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር እንዳንኖር ሊያግዱን እና እንቅፋት ይሆኑብናል። በጠላት ሀገር ውስጥ እንዳሉ ጥቂት ወዳጆችና ብዙ ጠላቶች እንዳላቸው ወታደሮች ነን።
እግዚአብሔር መንፈሳዊውን ጦርነት እንድናሸንፍ ይፈልጋል። ፀሎት ከአዛዥያችን ጋር የምንገናኝበት መንገድ ነው።
በጦርነት ውስጥ ትእዛዙን ችላ ብሎ በራሱ መንገድ ለመሄድ የወሰነን አንድ ወታደር አስብ። ከመልካም ይልቅ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፣ በእርሱ ላይ ጥገኛ የሆኑትን ሰዎች መርዳት ይሳነዋል እና ምናልባት ሊገደል ወይም ሊማረክ ይችላል።
በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ (ኤፌሶን 6:18)።
ይህ ጥቅስ የሚመጣው ጳውሎስ የአንድን አማኝ መንፈሳዊ የጦር እቃ በጊዜው በነበረው የጦር ትጥቅ ባሳየበት ክፍል መጨረሻ ላይ ነው። ጠላቶቻችን ሥጋዊ ሳይሆኑ መንፈሳዊ ናቸው ብሏል።
ምናልባት በዚያን ጊዜ ሬዲዮ ለወታደሮች የነበረ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ የመንፈሳዊውን ወታደር መሣሪያ ሌላው ክፍል ይኸውም ጸሎትን በምሳሌ ለማስረዳት ይጠቀምበት ነበር። ጳውሎስ የጦር ትጥቆችን ከገለጸ በኋላ ፀሎትን ከመንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ጋር መጠቀም እንዳለብን ተናግሯል።
ከመንፈሳዊ ክፋት ጋር በመዋጋት ላይ ስንቆም፣ መጸለይ አለብን ከአዛዥያችን ጋር መነጋገር አለብን። በጸሎት እንድንተጋ፣ ነቅተን እንድንጸና ተጠርተናል።
እግዚአብሔር ለሚሰሙት ሰዎች ምሪትን ቃል ገብቷል።
በፍጹም ልብህ በ እግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል (ምሳሌ 3:5-6)።
የሰው አካሄድ በ እግዚአብሔር ይጸናል፤ በመንገዱ ደስ ይለዋል (መዝሙረ ዳዊት 37:23)።
የክርስቶስ ተከታይ ውሳኔን እንደ ዓለም ሰዎች አያደርግም። አንዳንድ ሰዎች የሚመሩት በራሳቸው ፍላጎት እና ምኞት ብቻ ነው። እነሱም “ለእኔ ትክክል የሆነውን ማድረግ አለብኝ” ይላሉ። ሌሎች ሰዎች እንዲቆጣጠሩአቸው ከመፍቀድ ይልቅ የራሳቸውን ፍላጎት በቅድሚያ ማጤን አለብን ማለታቸው ነው። ነፃነት ማለት ራስ ወዳድ መሆን ማለት ነው ብለው ያስባሉ። የክርስቶስ ተከታዮች እግዘብሔርን ለማስደሰት እና ሌሎችን በሕይወታቸው ለመባረክ ስለሚፈልጉ ይለያሉ።
አንዳንድ ሰዎች ለሁሉም መልሶች ወደ ራሳችን እንድንመለከት ይመክሩናል። ስሜታችን እና ተፈጥሯዊ ባህሪያት ለውሳኔዎች በቂ መመሪያ እንደሆነ ያምናሉ። ወጣቶች ወግን እና የአረጋውያንን ምክር ችላ እንዲሉ ያበረታታሉ። ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርን ይንቃሉ። እንዲህ ዓይነቱ ምክር በዘመናዊ የሆሊዉድ መዝናኛ ውስጥ ታዋቂ ነው። የራሳቸውን ህልም ለመከተል በስልጣን እና በባህል ላይ በማመፅ የተሳካለትን ወጣት ታሪክ ያቀርባሉ። እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች ወደ ሀዘንና አደጋ እንደሚመሩ እውነቱን አያሳዩም።
በአንዳንድ ባህሎች የግለሰብ ውሳኔዎች በቤተሰብ ወይም በብሔር ወይም በጎሳ የተገደቡ ናቸው። ግለሰቦች ከቡድኑ እውቅና ውጪ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ፣ ስራቸውን እንዲቀይሩ፣ ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ወይም ጋብቻ እንዲፈጽሙ አይጠበቅባቸውም። በዚያ አካባቢ ውስጥ በጣም አስቸጋሪው ለውጥ አንድ ሰው ሃይማኖቱን መለወጥ ነው። አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ከሆነና ሕዝቡ በማይረዱት መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ከሆነ ስደት ሊደርስበት ይችላል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ አማኝ ጥበብ እና ምሪትን ለማግኘት መጸለይ አለበት።
የእግዚአብሔር ምሪት ሁል ጊዜ እንፈልጋለን እና እርሱ ሁልጊዜ ባላወቅናቸው መንገዶች እየመራን ነው። እርሱን በማናስበው ጊዜ እንኳን እርሱ ፈጽሞ አይረሳንም። ነገር ግን በተለይ የእርሱን ምሪት መፈለግ እና ምርጫዎችን በትክክል ለማየት እንዲረዳን ልንጠይቀው የሚገባን ጊዜ አለ። እግዚአብሔር ባልጠበቅነው መንገድ አካሄዳችንን ሊለውጥ ይፈልግ ይሆናል።
► ከእግዚአብሔር ልዩ አቅጣጫን የምንፈልግባቸው አንዳንድ ጊዜያት የትኞቹ ናቸው?
ከእግዚአብሔር አቅጣጫን መፈለግ አለብን፦
1. ሕይወትን የሚቀይሩ ውሳኔዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ፦ ጋብቻ፣ ሥራ፣ ትምህርት፣ ለሀገር ውስጥ ቤተክርስቲያን ቁርጠኝነት።
2. ተግባራዊ ውሳኔዎችን ሲያደርጉ፦ የሥራ ዕድሎች፣ የት እንደሚኖሩ፣ትልቅ ግዢዎች።
3. አገልግሎትን ሲያቅዱ እና ሲሰሩ፦[1] የአንድ ሰው የግል ጥሪ፣ የትና ከማን ጋር እንደሚያገለግሉ፣ የምንሰብከው እና የምናስተምረው ጭብጥ።
4. በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሲሳተፉ፦[2] እንዴት እንደሚያመልኩ፣ ምን እንደሚማሩ፣ ምን እንደሚሰጡ፣ እንዴት በምድር ላይ የክርስቶስ አካል መሆን እንደሚችሉ።
(1) በፀሎት ወደ እግዚአብሔር ቅረብ (ፊልጵስዩስ 4፥6)። አብዛኛው ህይወታችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ከምታደርጉአቸው ንግግሮች ጋር ግንኙነት ከተቋረጠ የራሳችሁን ዝንባሌዎች እና ውሱን አመለካከቶች እየተከተላችሁ ነው።
(2) ከግልፅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በላይ በራስህ ምክንያት አትታመን። ከላይ ያለው ጥቅስ እንደሚለው “በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” (ምሳሌ 3፥5)።
(3) የእግዚአብሄር ፈቃድ እንዲሆን የምታውቁትን ሁል ጊዜ ታዘዙ። ይህ ግንዛቤዎን ያሻሽላል። ለእግዚአብሔር ቃል የማይታዘዝ ሰው በእውነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ አይፈልግም ምክንያቱም እግዚአብሔር ፈቃዱን የሚገልጸው በቅዱስ ቃሉ ነው። ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ የምታውቁትን በከፊል ብቻ ብትታዘዙ፣ የበለጠ ግራ ትጋባላችሁ ብርሃኑም ወደ ጨለማ ይለወጣል (ሉቃስ 11፥35)።
እኛ ይህን ማድረጋችን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ እናውቃለን፡-
መስቀላችንን በየቀኑ ተሸክመን ኢየሱስን መከተል (ሉቃስ 9፥23)
ትክክል ማድረግ እና እውነትንም በልባችን መናገር (መዝሙረ ዳዊት 15፥2)
ታማኝ መንፈሳዊ መሪዎችን አክብር (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥12-13)።
ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥16)።
ሳታቋርጡ ጸልዩ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥17)።
በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥18)።
የመንፈስን እሳት አታዳፍኑ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥19)።
ትንቢትን አትናቁ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥20)።
ሁሉን ነገር ፈትኑ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥21)።
መልካም የሆነውን ያዙ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥21)።
ከማንኛውም ዐይነት ክፉ ነገር ራቁ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥22)።
ሙሉ በሙሉ ተቀደሱ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥23)።
እና በአንድ ቃል የተጠቃለሉ ሌሎች ብዙ ትእዛዞች አሉ፦ ፍቅር (ሮሜ 13፥8-10)። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የምናውቀውን ስናደርግ ብዙም ጠቃሚ ያልሆኑ ውሳኔዎቻችን ግልጽ ይሆናሉ።
(4) ትዕግስተኛ ሁኑ። እግዚአብሔር በሮችን ሲከፍት እና ሁኔታዎችን ሲያዘጋጅልዎት መጠበቅ ሊኖርብዎ ይችላል። በትዕግስት ማጣት ምክንያት ቶሎ ውሳኔዎችን አታድርጉ። “በ እግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል” (መዝሙረ ዳዊት 37፥7)። በጥድፊያ ስሜት የተነሳ ስህተት እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር በጭራሽ አያድርጉ።
(5) ጥሩ ምክርን አድምጡ “ጦርነት ለመግጠም መልካም ምክር፣ ድል ለማድረግም ብዙ አማካሪዎች ያስፈልጋሉ” (ምሳሌ 24፥6)። እግዘብሔር ትልቅ ውሳኔ እንድታደርጉ በሚፈልግበት ጊዜ በሕይወታችሁ ውስጥ አስፈላጊ ለሆኑ ሌሎች ሰዎችም ጭምር ብዙ ጊዜ ያሳያቸዋል። አንተን የሚያውቁህ እና የሚያስቡልህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው አረጋውያን ካሉ ስህተት ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማድረግ በቀላሉ መወሰን የለብህም።
► በእግዚአብሔር እንደተመራ የሚያውቁትን የውሳኔዎትን ምሳሌ አካፍሉ። እግዚአብሔር ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ያሳዮት እንዴት ነው?
► የተሳሳተ ውሳኔዎትንም ምሳሌ ቢያካፍሉ ጠቃሚ ነው። በእግዚአብሔር በተሻለ ለመመራት ከአምስቱ መርሆዎች አንዱን መከተል ተስኖታል?
ሌሎችም በተመሳሳይ እንዲያጋሩ ይፍቀዱ።
ታሪኩ እንደ ተነገረው Charles Stalker የሚባል ሰባኪ አንድ ቀን ጠዋት ሲጸልይ እግዚአብሔር እነዲህ ሲል ተናገረው “ወደ ቻይና እንድትሄድ እፈልጋለሁ”። Stalker የሚሄድበት አድራሻም ሆነ ገንዘብ ስለሌለው ተገረመ። ስሜቱ በጣም ጠንካራ ስለነበር ሻንጣውን ጠቅልሎ እንዲህ አይነት ጉዞ ወደሚጀመርበት ጣቢያ ሄደ። አንድ እንግዳ ወደ እርሱ ቀረበና “አንተ Charles Stalker ነህ?” ሲል ጠየቀው። ከዚያም “ወደ ቻይና ልልክህ ትኬት ይዤ ነው የተላኩት” ብሎ ቀጠለ።
► እግዚአብሔር ፈቃዱን እንዲያሳየን መጠበቅ ያለብን በዚህ መንገድ ነውን? በዚህ መንገድ ለሚያደርጋቸው ውሳኔዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማግኘት የሚጠብቅ ሰው ችግር ሊገጥመው ይችላልን?
አንዳንድ ሰዎች ለሚያደርጉት ውሳኔ ሁሉ መንፈሳዊ የሆኑ አቅጣጫዎችን ይጠብቃሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሁሉም አመለካከቶች እና ሁኔታዎች ጋር ተቃራኒ ሊሆን እንደሚችል ስለሚገምቱ መደበኛውን ምክንያታዊነት እና ሁኔታዎችን ችላ ይላሉ።
እግዚአብሔር ለውሳኔዎቻችን መንፈሳዊ የሆነ መገለጥን መስጠት አለበት ብለን አጥብቆ መናገሩ ስህተት ነው ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ፈቃዱን በዚህ መንገድ አያሳይም። አንድ ሰው ማመዛዘንን እና ሁኔታዎችን ችላ ሲል ከእግዚአብሔር መመሪያ እንዳገኘ ያስብ ይሆናል እውነታው ግን የራሱን ስሜት ወይም ምናብ እየተከተለ ነው።
አንድ ነገር በመፅሐፍ ቅዱስ በግልጽ የታዘዘ ወይም የተከለከለ በሚሆንበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እናውቃለን። ነገር ግን በህይወታችን ውስጥ የተለየ ያልታዘዙ ወይም ያልተከለከሉ አማራጮች ያሉን ብዙ ውሳኔዎች አሉ። አንድ ሰው የት መኖር እንዳለበት፣ ምን ዓይነት ሥራ ሊኖረው እንደሚገባ እና ገንዘቡን እንዴት ማውጣት እንዳለበት እንዴት ማወቅ ይችላል?
► ልዩ መገለጥ ከሌለ አንድ ሰው በመፅሐፍ ቅዱስ በተለየ ላልተመራ ውሳኔ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት ሊያውቅ ይችላል?
አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔር ፈቃድ ከምክንያታዊነት እና ከሁኔታዎች ውጭ ከተፈጥሮ በላይ በሆነ መንገድ መገለጥ አለበት ብለው ስለሚጠብቁ እግዚአብሔር ምሪት ለመስጠት ይጠቀምባቸዋል ብለው የሚያስቡትን ምክንያታዊ ያልሆነ ዘዴ ያገኛሉ። ፈቃዱን ለማሳየት አንድ ምልክት እንዲሰጥ እግዚአብሔርን ይጠይቁ ይሆናል። ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ከሁኔታቸው ጋር የሚስማማ የዘፈቀደ ጥቅስ ሊከፍቱ ይችላሉ።
John Wesley የእግዚአብሔር ፈቃድን እንዴት መለየት እንደሚቻል አንዳንድ ተግባራዊ መመሪያዎችን ሰጥቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሔር አጠቃላይ ፈቃድ ቅዱሳን እንድንሆን እና መልካም ነገሮችን እንድናከናውን እንደሆነ እናውቃለን ብሏል። ስለዚህ አንድ የተወሰነ ውሳኔ ለማድረግ የትኛው አማራጭ ቅዱሳን እንድንሆን የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ውጤታማነታችንን ከፍ የሚያደርግልንን መምረጥ አለብን።
ከተሞክሮ የትኞቹ ሁኔታዎች በመንፈሳዊ እንደሚረዱን እና የትኞቹ አደገኛ እንደሆኑ እንማራለን። አንዳንድ ሁኔታዎች ለሁሉም በመንፈሳዊ አደገኛ ናቸው፤ ሌሎች ለአንዳንድ ሰዎች አደገኛ ናቸው ነገር ግን ለሁሉም አይደለም። በቻልነው መጠን በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድንሆን በሚረዱን ሁኔታዎች ውስጥ ራሳችንን እናስገባ እና ወደ ፈተና ከሚወስዱን ሁኔታዎች መራቅ አለብን (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥12-13)።
በምክንያትና በተሞክሮ እና በሌሎች ምክር የትኛው አማራጭ ውጤታማነታችንን እንደሚያሳድግ ልንገነዘብ እንችላለን።
እግዚአብሔር ፈቃዱን በልዩ መገለጥ አያሳይም። በጥንቃቄ ስናስብና ሁኔታዎችን በምንመረምርበት ጊዜ መፅሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎችን እንድንጠቀም ይጠብቅብናል። ባናውቀውም እንኳ መንፈስ ቅዱስ ይመራናል። ለአብዛኛዎቹ ውሳኔዎች መገለጥን መጠበቅ የለብንም ነገር ግን ለጥበብ እና ለማስተዋል መጸለይ ነው።
ከእግዚአብሔር የተለየ መመሪያ እናገኛለን የሚሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎችን ለመስማት ፈቃደኛ አይሆኑም (ምሳሌ 12፥15)። ሰዎች ውሳኔያቸውን ሲጠይቁ ሊናደዱ ይችላሉ። ትህትናን ሳይሆን ትዕቢትን እና ግትርነትን ያሳያሉ።
► አንድ ተማሪ ለብድኑ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥5-6 ያንብብ።
ባልተለመደ ሁኔታ ካልሆነ በቀር አንድ ሰው እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት በትክክል አሳውቆኛል ብሎ ባይናገር ይሻላል። አንድ ሰው ይህን ሲናገር ማንም ሰው ምክር ወይም አስተያየት መስጠት ይከብደዋል። በእግዚአብሔር እርዳታ የተሻለውን ውሳኔ ለማድረግ እየጣረ እንደሆነ ቢናገር ይሻለዋል።
Wesley ከሰጠው መርሆች በተጨማሪ፣ ስለአማራጮችዎ ሲያስቡ እነዚህን ግምት ውስጥ ያስገቡ ብሏል፦
1. ግልጽ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዞች ጋር ይስማማልን? እግዚአብሔር ቃሉን እንዳትታዘዙ በፍጹም አይፈልግም።
2. መፅሐፍ ቅዱስ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ጋር ይስማማልን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ያሳየናል። ውሳኔህ መጀመሪያን ሊሆኑ የሚገባቸውን ነገሮች ያስቀድማልን?
3. ከሁኔታዎች ተጨባጭ እይታ ጋር ይጣጣማልን? ለዚህ ውሳኔ እግዚአብሔር ሁኔታዎን እንዴት ሲያዘጋጅ እንደነበረ ማየት መቻል አለብዎት።
4. ምክንያታዊ ነውን? እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ምክንያታዊ የማይመስል ነገር እንድታደርግ ይመራሃል፤ ነገር ግን እንደዚህ ሲሆን ደግሞ ፈቃዱን ግልጽ ያደርጋል። የእግዚአብሔርንን ፈቃድ እንድታስተውል በሚል ምክንያትን ፈጽሞ አትተው።
5. አምላካዊ ባህሪ ነውን? ማንኛውም ሁኔታ በጣም ልዩ ነው ብለው እግዚአብሔር የማያስደስት ነገር ላደርግ እችላለሁ በለው አያስቡ።
6. ሌሎችን እንደ ራስህ ከመውደድ ጋር ይስማማልን? የራስ ወዳድነት ስሜት ማስተዋልን ያዛባል።
7. ጥሩ ተጽእኖ ይኖረዋልን? ሌሎች እርስዎ እንዳደረጉት ቢያደርጉስ? ይህ ጥሩ ነውን?
8. በአምላካዊ አማካሪዎች የተረጋገጠ ነውን? ከእኛ ጋር የሚስማሙ ጓደኞች እንዴት ማግኘት እንደምንችል ሁላችንም እናውቃለን ነገር ግን በጣም መንፈሳዊ እና ጥበበኛ የሚመስሉ ሰዎች ስለ ውሳኔዎ ምን ይላሉ?
የእግዚአብሔር ፈቃድ በጣም ያልተለመደ ነገር ከሆነ ከጥርጣሬ በላይ ለአንተ ሊያሳውቅህ ይችላል። መልአክ ወይም ራዕይ ወይም የሚቃጠል ቁጥቋጦ ባለፈው ጊዜ ለአንዳንድ ሰዎች እርግጠኝነትን ሰጥቷል። እግዚአብሔር በቀላሉ ከጥርጣሬ በላይ የሆነ ውስጣዊ ማረጋገጫን ሊሰጥ ይችላል። ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር የተላከ ግልጽ መልእክት ካልደረሰህ ትክክለኛውን አማራጭ ለማወቅ አስተማማኝ መመሪያዎችን መከተል አለብህ። ለእያንዳንዱ ውሳኔ ልዩ መገለጥ ለመቀበል አትጠብቅ። በቅንነት እና በፀሎት ትክክለኛ የሆኑ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች ካሰላሰሉ እግዚአብሔር ውሳኔዎን ለመምራት ታማኝ ይሆናል።
በሮሜ 12፥1-2 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው። መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እነዚህ ጥቅሶች የአንድ ሰው መንፈሳዊ ሁኔታ ውሳኔውን እንዴት እንደሚነካ ያሳያሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማግኘት አንድ ሰው በመጀመሪያ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መሰጠት አለበት። የአማኝ ውሳኔዎች ከአለም ውሳኔዎች ጋር ይቃረናሉ ምክንያቱም አማኙ ከአለም ጋር አይመሳሰልም ነገር ግን የተለወጠ እና ውሳኔዎችንም በአዲስ አእምሮ ያደርጋል።
የእግዚአብሔርን መመሪያ በማስተዋል ረገድ በጣም አስፈላጊው የተነሳሽነት ምክንያቶች ናቸው። በውሳኔው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ብቻ የሚፈልግ ሰው ግራ ሊጋባ ይችላል። አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፅሐፍ ቅዱስ እና በምክንያታዊ መንገዶች ከፈለገ እና ይህን ለማድረግ በሙሉ ልብ ቁርጠኝነት ውሳኔ ካደረገ የእግዚአብሔር ፈቃድ አያመልጠውም።
► ስለ Wesley መርህ አንዳንድ አተገባበር ተወያዩ። አንዳንዶቹ ምሳሌዎችም ጊዜ ለማሳለፍ የጓደኞች ምርጫ፣ የስራ አማራጮች ወይም የፍቅር ግንኙነት (ያላገባ ከሆነ) ሊሆኑ ይችላሉ። “ቅዱስ እንድሆን የሚረዳኝና ውጤታማነቴን ከፍ ለማድረግ የሚረዳኝ የትኛው ሁኔታ ነው?” የሚለውን ግምት ውስጥ ያስገብ።
► አንዳንድ ሰዎች ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ሲሆኑ ወይም በአንዳንድ ቦታዎች ክርስቲያናዊ ማንነታቸውን የሚጠብቁ አይመስሉም። ምሳሌዎችን በመስጠት ተመልከቱ።
► ሌሎች ለውይይት የሚሆኑ ነጥቦች፦
በውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ የማበረታቻዎች ሚና
ምልክትን በመጠበቅ ላይ ያለው ስህተት
ውስጣዊ ስሜቶችን ከመጠን በላይ የመተማመን አደጋ
የሰማይ አባት
ለእኔ ጥሩ ነገሮችን ስላቀድክልኝ አመሰግናለሁ። ከማየው በላይ አንተ የእኔን እርምጃ እየመራህ እንደሆነ አውቃለሁ።
በፀሎት ወደ አንተ እንድቀርብ እርዳኝ። ለምታሳየኝ እውነት ትኩረት እንድሰጥ እርዳኝ።
ቅዱስ መሆን እና ለክብርህ የምችለውን ሁሉ ማከናወን እፈልጋለሁ።
ከፈቃድህ እንዳያርቁኝ መነሳሳቶቼን ንጹሕ አድርግ። በህይወቴ ውስጥ እንዳስቀመጥካቸው ጥበበኛ አማካሪዎች ምራኝ።
በእያንዳንዱ ውሳኔ ላይ ልታመንህ እፈልጋለሁ። በሙሉ ልቤ በመታዘዝ ፈቃድህን መከተል እፈልጋለሁ።
ለእኔ ጥሩውን ስለፈለግክ አመሰግናለሁ።
አሜን
(1) ምሳሌ 3፥1-12ን አጥና። በዚህ ክፍል ስለ ተገለጹት ቅድሚያዎች፣ አመለካከቶች እና ባህሪያት ጻፍ። እነዚህን ባህሪያት እንዴት በግልዎ ማዳበር እንደሚችሉ ይጻፉ። (በአጠቃላይ 1-2 ገጾችን መጻፍ አለብዎት።)
(2) ያዕቆብ 4፥13-17ን ይመልከቱ። በሁኔታዎች ላይ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት አስተውል። በቁጥር 16 ላይ የተጠቀሰው “ትዕቢት” ምንድን ነው? ይህ ምንባብ ስለወደፊቱ እቅድ ስለማውጣት ምን እንደሚነግረን የሚገልጽ አንቀጽ ጻፍ።
(3) በፀሎትና በውሳኔ አደራረግ መካከል ያለውን ዝምድና የሚገልጹ ሁለት አንቀጾችን ጻፍ። እነዚህን ጥያቄዎች መልሱ፦
ፀሎት በውሳኔያችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?
ከፀሎት እና ውሳኔ አደራረግ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ስህተቶች ምንድናቸው?
13 lessons · አማርኛ
Your print request has been recorded. Your download should begin shortly.
Download Print-Ready FileFree to print for ministry use. No changes to content, no profit sales.
SGC exists to equip rising Christian leaders around the world by providing free, high-quality theological resources. We gladly grant permission for you to print and distribute our courses under these simple guidelines:
All materials remain the copyrighted property of Shepherds Global Classroom.
Questions? info@shepherdsglobal.org
Total
$21.99Added to Cart!
By submitting your contact info, you agree to receive occasional email updates about this ministry.
Download audio files for offline listening
No audio files are available for this course yet.
Check back soon or visit our audio courses page.
Share this free course with others